12 ከነቢዩ ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም መጣ፤“የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንተ በአባትህ በኢዮሣፍጥ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህም፤
13 ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደሃል፤ የአክዓብ ቤት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲያመነዝር እንዳደረገ ሁሉ፣ አንተም ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲያመነዝሩ አሳሳትሃቸው፤ እንዲሁም ካንተ የሚሻሉትን፣ የገዛ ወንድሞችህንና የአባትህን ቤተ ሰብ አባላት ገደልሃቸው፤
14 ስለዚህ እነሆ፤ እግዚአብሔር ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ያለህን ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይመታል።
15 አንተም ራስህ በየዕለቱ እየባሰ በሚሄድ የአንጀት በሽታ ክፉኛ ትታመማለህ፤ በመጨረሻም ሕመሙ አንጀትህን ወደ ውጭ ያወጣዋል።”
16 እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩ ዐረቦችን በኢዮሆራም ላይ በጠላትነት እንዲነሡ አደረገ።
17 እነርሱም በይሁዳ ላይ ወጡ፤ ወረሯትም። በንጉሡ ቤተ መንግሥት የሚገኘውን ዕቃ ሁሉ፣ ከወንዶች ልጆቹና ከሚስቶቹ ጋር ወሰዱ፤ ከመጨረሻ ልጁ ከአካዝያስ በስተቀር አንድም ልጅ አልቀረለትም።
18 ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር ሊድን በማይችል የአንጀት በሽታ ኢዮሆራምን ቀሠፈው።