2 ዜና መዋዕል 24:5-11 NASV

5 ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦም፣ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በየዓመቱ ለማደስ ገንዘብ ከእስራኤል ሁሉ ሰብስቡ፤ ይህንንም አሁኑኑ አድርጉት” አላቸው። ሌዋውያኑ ግን ቸል አሉ።

6 ስለዚህ ንጉሡ ሊቀ ካህኑን ዮዳሄን ጠርቶ፣ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴና የእስራኤል ጉባኤ ለምስክሩ ድንኳን እንዲወጣ የወሰኑትን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላተጋሃቸው ለምንድን ነው?” አለው።

7 በዚህ ጊዜ የዚያች ክፉ የጎቶልያ ልጆች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሰብረው በመግባት የተቀደሱ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ለበኣል ጣዖታት አገልግሎት እንዲውሉ አድርገው ነበር።

8 በንጉሡም ትእዛዝ የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በር አጠገብ በውጭ በኩል አኖሩት።

9 ከዚህ በኋላ እስራኤል በምድረ በዳ ሳሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ።

10 ሹማምቱ ሁሉ፣ ሕዝቡም ሁሉ ግብሩን በደስታ አመጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጨመሩ።

11 ሣጥኑ በሌዋውያኑ እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በሚደርስበት ጊዜ፣ እነርሱም በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም ይመጡና ሣጥኑን አጋብተው ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። ይህን በየቀኑ በማድረግ እጅግ ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ።