2 ዜና መዋዕል 26:12-18 NASV

12 በተዋጊዎቹ ላይ የተሾሙት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ጠቅላላ ቊጥር ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር።

13 በእነዚህም የሚመራ ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሰው ያለው ሰራዊት አለ፤ ይህም ንጉሡ በጠላቶቹ ላይ በሚያደርገው ዘመቻ ለመሰለፍ የሚበቃ ጠንካራ ኃይል ነበር።

14 ዖዝያን ለሰራዊቱ ሁሉ ጋሻ፣ ጦር፣ የራስ ቁር፣ ጥሩር፣ የቀስት ማስፈንጠሪያ ደጋንና የሚወነጨፍ ድንጋይ አደለ።

15 በኢየሩሳሌምም፣ ንድፎቻቸው በባለ ሙያዎች የተዘጋጁ፣ በመጠበቂያ የግንብ ማማዎችና በየማዕዘኑ መከላከያዎች ላይ ፍላጻ የሚስፈነጠርባቸውንና ትልልቅ ድንጋዮች የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አሠራ። እስኪበረታም ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስለታገዘ፣ ዝናው በርቀትና በስፋት ተሰማ።

16 ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ እግዚአብሔርን በደለ፤

17 ካህኑም ዓዛርያስ ቈራጥ ከሆኑ ከሌሎች ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ጋር ተከትሎት ገባ።

18 እነርሱም ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ “ዖዝያን ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ማጠን ለተለዩትና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ እንጂ ለአንተ የተገባ አይደለም፤ እግዚአብሔርን በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድም ክብር አይሆንልህምና” አሉት።