2 ዜና መዋዕል 27:1-7 NASV

1 ኢዮአታም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እናቱም ኢየሩሳ የተባለች የሳዶቅ ልጅ ነበረች።

2 አባቱ ዖዝያን እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ይሁን እንጂ እንደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አልገባም። ሕዝቡም በበደሉ እንደ ገፋበት ነበር።

3 ኢዮአታም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የላይኛውን በር እንደ ገና ሠራው፤ በዖፌልም በኩል ባለው ቅጥር ላይ፣ አያሌ የማሻሻል ተግባር አከናወነ።

4 በይሁዳ ኰረብታዎች ላይ ከተሞችን፣ ደን በለበሱ ስፍራዎችም ምሽጎችንና ማማዎችን ሠራ።

5 ኢዮአታም የአሞናውያንን ንጉሥ ወግቶ ድል አደረጋቸው። በዚያ ዓመትም አሞናውያን አንድ መቶ መክሊት ጥሬ ብር፣ ዐሥር ሺህ ቆሮስ ስንዴና ዐሥር ሺህ ቆሮስ ገብስ ገበሩለት። አሞናውያን በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ይህንኑ ግብር አመጡለት።

6 ኢዮአታም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ስለተመላለሰ፣ እየበረታ ሄደ።

7 በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ያደረጋቸው ጦርነቶችና የሠራቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል።