2 ዜና መዋዕል 29:17-23 NASV

17 ማንጻቱንም በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ጀምረው በዚያኑ ወር በስምንተኛው ቀን እስከ መቅደስ ሰበሰብ ደረሱ፤ በሚቀጥሉትም ስምንት ቀናት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ፤ የመቀደሱም ሥራ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

18 ከዚያም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉ፤ “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሙሉ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ከነዕቃዎቹ ሁሉ፣ ኀብስተ ገጹ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛ፣ ከነዕቃዎቹ አንጽተናል።

19 ንጉሥ አካዝ ነግሦ ሳለ ታማኝነቱን ትቶ፣ ከቦታቸው ያነሣቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ቀድሰናቸዋል፤ እነሆ፤ ዕቃዎቹ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያ ፊት ለፊት ናቸው።”

20 በማግስቱም ጧት በማለዳ፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማዪቱን ሹማምት በአንድነት ሰብስቦ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ፤

21 እነርሱም ስለ መንግሥቱ፣ ስለ መቅደሱና ስለ ይሁዳ ሰባት ወይፈኖች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት የፍየል ጠቦቶች ለኀጢአት መሥዋዕት አቀረቧቸው፤ ንጉሡም እነዚህን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቡ የአሮንን ዘሮች ካህናቱን አዘዘ።

22 ካህናቱም ወይፈኖቹን ዐርደው ደሙን በመውሰድ በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ እንደዚሁም ጠቦቶቹን ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት።

23 ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትን ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እነርሱም እጆቻቸውን ጫኑባቸው።