1 ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በሞሪያ ተራራ ላይ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ዳዊት ባዘጋጀው ቦታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ።
2 በነገሠም በአራተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በሁለተኛው ቀን ቤተ መቅደሱን መሥራት ጀመረ።
3 ሰሎሞን ለሕንጻው የጣለው መሠረት በቀድሞው ስፍር ልክ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር።
4 በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ላይ ያለው በረንዳ ርዝመቱ በቤተ መቅደሱ ወርድ ልክ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ከፍታውም ሃያ ክንድ ነበር። ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።
5 የቤተ መቅደሱን ዋና ክፍል በጥድ እንጨት አልብሶ በተጣራ ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳልም ቀረጸበት።
6 ቤተ መቅደሱን በከበረ ድንጋይ አስጌጠው፤ የተጠቀመበትም ወርቅ የፈርዋይም ወርቅ ነበር።
7 የጣራውን ተሸካሚዎች፣ መቃኖችን፣ የቤተ መቅደሱን ግድግዳና መዝጊያዎች በወርቅ ለበጠ፤ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቤልን ምስል ቀረጸ።