4 በቤተ መቅደሱ መግቢያ በር ላይ ያለው በረንዳ ርዝመቱ በቤተ መቅደሱ ወርድ ልክ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ከፍታውም ሃያ ክንድ ነበር። ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።
5 የቤተ መቅደሱን ዋና ክፍል በጥድ እንጨት አልብሶ በተጣራ ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳልም ቀረጸበት።
6 ቤተ መቅደሱን በከበረ ድንጋይ አስጌጠው፤ የተጠቀመበትም ወርቅ የፈርዋይም ወርቅ ነበር።
7 የጣራውን ተሸካሚዎች፣ መቃኖችን፣ የቤተ መቅደሱን ግድግዳና መዝጊያዎች በወርቅ ለበጠ፤ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቤልን ምስል ቀረጸ።
8 እንደዚሁም ቅድስተ ቅዱሳኑን ሠራ፤ ርዝመቱ ከቤተ መቅደሱ ወርድ ጋር እኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ስፋቱም ሃያ ክንድ ነበር፤ ውስጡንም በስድስት መቶ መክሊት የተጣራ ወርቅ ለበጠው።
9 የወርቅ ምስማሮቹም አምሳ ሰቅል ይመዝኑ ነበር፤ የላይኛውንም ክፍሎች እንደዚሁ በወርቅ ለበጠ።
10 በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የሁለት ኪሩቤል ምስል አስቀርጾ በወርቅ ለበጣቸው።