2 ዜና መዋዕል 30:1-7 NASV

1 ሕዝቅያስ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲመጡ፣ ለመላው እስራኤልና ለይሁዳ መልእክት ላከ፤ ለኤፍሬምና ለምናሴም ደብዳቤ ጻፈ።

2 ንጉሡ፣ ሹማምቱና መላው የኢየሩሳሌም ጉባኤ የፋሲካውን በዓል በሁለተኛው ወር ለማክበር ተስማሙ።

3 በቂ ካህናት ራሳቸውን ስላል ቀደሱና ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተ ሰበሰቡ፣ በዓሉን በወቅቱ ለማክበር አልቻሉም ነበር።

4 ንጉሡና መላው ጉባኤም ዕቅዱ ትክክል ሆኖ አገኙት።

5 ስለዚህ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር ሕዝቡ እንዲመጣ፣ ከቤርሳቤህ እስከ ዳን ድረስ ዐዋጅ እንዲነገር ወሰኑ፤ በተጻፈው መሠረት በዓሉ ብዛት ባለው ሕዝብ ተከብሮ አያውቅም ነበርና።

6 መልእክተኞችም በንጉሡ ትእዛዝ፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እርሱ ወደ ተረፋችሁት፣ ከአሦር ነገሥታትም እጅ ወዳመለጣችሁት፣ ወደ እናንተ እንዲመለስ እናንተም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።

7 እንደምታዩት ሁሉ መሣለቂያ እስኪያደርጋቸው ድረስ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ።