2 ዜና መዋዕል 30:16-22 NASV

16 ከዚያም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደታዘዘው መደበኛ ቦታቸውን ያዙ። ካህናቱም ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ።

17 ከጉባኤው መካከል አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያልቀደሱ ስለ ነበሩ፣ ሌዋውያኑ በሥርዐቱ መሠረት ራሳቸውን ላላነጹትና ጠቦቶቻቸውን ለእግዚአብሔር መቀደስ ላልቻሉት ሁሉ የፋሲካውን በጎች ማረድ ነበረባቸው።

18 ምንም እንኳ ከኤፍሬም፣ ከምናሴ፣ ከይሳኮርና ከዛብሎን ከመጡት አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያላነጹ ቢሆንም ከተጻፈው ትእዛዝ ውጭ ፋሲካውን በሉ። ሕዝቅያስ ግን እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ቸሩ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይቅር በላቸው፤

19 ምንም እንኳ በመቅደሱ ሥርዐት መሠረት የነጹ ሆነው ባይገኙም የአባቶቻቸው አምላክ የሆነውን እግዚአብሔር አምላካቸውን ለመፈለግ ልባቸውን የሚያዘጋጁትን ሁሉ ይቅር በላቸው።”

20 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም ፈወሰ።

21 ሌዋውያኑና ካህናቱ በእግዚአብሔር የዜማ ዕቃ ታጅበው፣ በየዕለቱ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት እስራኤላውያን የቂጣን በዓል በታላቅ ደስታ ለሰባት ቀን አከበሩ፤

22 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ በንግግሩ አበረታታ። ሰባቱንም ቀን የተወሰነላቸውን ድርሻ እየበሉና የኅብረት መሥዋዕቱንም እያቀረቡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።