2 ዜና መዋዕል 30:20-26 NASV

20 እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም ፈወሰ።

21 ሌዋውያኑና ካህናቱ በእግዚአብሔር የዜማ ዕቃ ታጅበው፣ በየዕለቱ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት እስራኤላውያን የቂጣን በዓል በታላቅ ደስታ ለሰባት ቀን አከበሩ፤

22 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ በንግግሩ አበረታታ። ሰባቱንም ቀን የተወሰነላቸውን ድርሻ እየበሉና የኅብረት መሥዋዕቱንም እያቀረቡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

23 ጉባዔውም ሁሉ በተከታዩ ሰባት ቀን በዓሉን እንደ ገና ለማክበር ተስማሙ፣ ስለዚህ በዓሉን ለሰባት ተጨማሪ ቀን በታላቅ ደስታ አከበሩ።

24 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ አንድ ሺህ ወይፈን፣ ሰባት ሺህ በግና ፍየል ለጉባኤው ሰጠ፤ ሹማምቱም እንደዚሁ አንድ ሺህ ወይፈን፣ ዐሥር ሺህ በግና ፍየል ሰጡ። እጅግ ብዙ ካህናትም ራሳቸውን ቀደሱ።

25 መላው የይሁዳ ጉባኤ፣ ካህናቱና ሌዋውያኑ፣ ከእስራኤል የተሰበሰበው ጉባኤ ሁሉ፣ እንዲሁም ከእስራኤል የመጡ መጻተኞችና በይሁዳ የሚኖሩ መጻተኞች ደስ አላቸው።

26 ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ጊዜ አንሥቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ በዓል ተደርጎ ስለማያውቅ፣ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ።