8 ሕዝቅያስና ሹማምቱም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ።
9 ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቃቸው፤
10 ከሳዶቅ ቤተ ሰብ የሆነው ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስም፣ “ሕዝቡ ስጦታውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማምጣት ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በቂ ምግብ አግኝተናል፤ ብዙም ተርፎናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለባረከም ይህን ያህል ብዛት ያለው ሊተርፍ ችሎአል” አለ።
11 ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ጎተራ እንዲያዘጋጁ አዘዛቸው፤ እነርሱም አዘጋጁ።
12 ከዚያም ስጦታውን፣ ዐሥራቱንና የተቀደሱ ስጦታዎቹን በታማኝነት አምጥተው አስገቡ። ሌዋዊው ኮናንያ የእነዚሁ ዕቃዎች ኀላፊ ሲሆን ወንድሙ ስሜኢ ደግሞ በማዕረግ ሁለተኛ ነበር።
13 ይሒዒል፣ ዓዛዝያ፣ ናሖት፣ አሣሄል፣ ይሬሞት፣ ዮዛባት፣ ኤሊኤል፣ ሰማኪያ፣ መሐትና በናያስ በንጉሡ ሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ በዓዛርያስ ተሹመው በኮናንያና በወንድሙ በሰሜኢ ሥር ሆነው ተቈጣጣሪዎች ነበሩ።
14 የምሥራቁ በር ጠባቂ የሆነው የሌዋዊው የይምና ልጅ፣ ቆሬ ደግሞ በበጎ ፈቃድ፣ ለእግዚአብሔር በቀረበው ስጦታ ላይ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትንም ነገሮች ለማከፋፈል፣ ኀላፊ ነበረ።