2 ዜና መዋዕል 32:7-13 NASV

7 “በርቱ፤ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና አብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም።

8 ከእነርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።

9 ከዚህ በኋላ ሰናክሬም ከሰራዊቱ ሁሉ ጋር ለኪሶን ከቦ ሳለ፣ የሚከተለውን መልእክት በጦር መኮንኖቹ አማካይነት፣ ለሕዝቅያስና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ ላከ፤

10 “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የሚለው ይህ ነው፤ በተከበበችው በኢየሩሳሌም እስከዚህ የቈያችሁት በማን ተማምናችሁ ነው?

11 ሕዝቅያስ፣ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል’ ማለቱስ በራብና በጥማት እንድትሞቱ ሊያስታችሁ አይደለምን?

12 ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ ‘በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በላዩም መሥዋዕት አቃጥሉ’ በማለት የራሱን አምላክ የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ያስወገደስ ሕዝቅያስ አይደለምን?

13 “እኔና አባቶቼ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁምን? ታዲያ የእነዚያ መንግሥታት አማልክት ምድራቸውን ከእጄ ለማዳን ችለዋልን?