1 ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አምሳ አምስት ዓመት ገዛ።
2 እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳዶ ያስወጣቸውን ሕዝቦች አስጸያፊ ልማድ በመከተልም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።
3 አባቱ ሕዝቅያስ ያጠፋቸውን የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ ለበአሊም መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ዐምዶች ሠራ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሰገደ፤ አመለካቸውም።
4 እግዚአብሔር፣ “ስሜ ለዘላለም በኢየሩሳሌም ይኖራል” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቀደስ መሠዊያዎችን ሠራ።
5 በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ፣ ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ።
6 በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቊጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።
7 ያበጀውን የተጠረበ ምስል ወስዶም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አኖረ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤