19 ጸሎቱና እግዚአብሔር ራርቶ ልመናውን እንዴት እንደ ተቀበለው፣ ኀጢአቱ ሁሉና ታማኝነቱን ማጒደሉ፣ እንደዚሁም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ያሠራቸው የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ያቆማቸው የአሼራ ምስል ዐምዶችና ጣዖታት ሁሉ በባለ ራእዮች መዛግብት ተጽፈዋል።
20 ምናሴም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱም ተቀበረ። ልጁም አሞን በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
21 አሞን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሁለት ዓመት ገዛ።
22 አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ አሞንም ምናሴ ያሠራቸውን ጣዖታት ሁሉ አመለከ፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው።
23 አሞን በእግዚአብሔር ፊት ራሱን እንዳዋረደ እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ራሱን አላዋረደም፤ ነገር ግን በበደል ላይ በደል እየጨመረ ሄደ።
24 የአሞን ሹማምት በእርሱ ላይ አሢረው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት።
25 ከዚያም ያገሩ ሕዝብ በንጉሡ አሞን ላይ ያሤሩትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በእርሱ ፈንታ አነገሡት።