2 ዜና መዋዕል 33:5-11 NASV

5 በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ፣ ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ።

6 በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቊጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።

7 ያበጀውን የተጠረበ ምስል ወስዶም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አኖረ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤

8 በሙሴ አማካይነት ያዘዝኋቸውን ሕግጋቴን፣ ደንቦቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽሙ እንጂ፣ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር የእስራኤላውያን እግር ከእንግዲህ ለቆ እንዲወጣ አላደርግም።”

9 ምናሴ ግን እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ዘንድ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ አሳተ።

10 እግዚአብሔር ለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።

11 ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሰራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ እነርሱም በምናሴ አፍንጫ መንጠቆ አገቡበት፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት።