2 ዜና መዋዕል 33:7-13 NASV

7 ያበጀውን የተጠረበ ምስል ወስዶም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አኖረ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤

8 በሙሴ አማካይነት ያዘዝኋቸውን ሕግጋቴን፣ ደንቦቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽሙ እንጂ፣ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር የእስራኤላውያን እግር ከእንግዲህ ለቆ እንዲወጣ አላደርግም።”

9 ምናሴ ግን እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ዘንድ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ አሳተ።

10 እግዚአብሔር ለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።

11 ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሰራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ እነርሱም በምናሴ አፍንጫ መንጠቆ አገቡበት፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት።

12 በተጨነቀም ጊዜ የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ።

13 ወደ እርሱም በጸለየ ጊዜ፣ በጭንቀት ልመናው ራርቶለት እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማው። ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ መንግሥቱም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዐወቀ።