2 ዜና መዋዕል 34:21-27 NASV

21 “ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ቅሬታዎች በተገኘው መጽሓፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ ታላቅ የእግዚአብሔር ቊጣ ፈስሶአል፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።”

22 ኬልቅያስና ንጉሡ ከእርሱ ጋር የላካቸው ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደሆነችው ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍለ ከተማ ትኖር ነበር።

23 ነቢይቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤

24 ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ በተጻፈው ርግማን ሁሉ መሠረት፣ በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ።

25 እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና እጃቸው በሠራው ነገር ሁሉ ለቊጣ ስላነሣሡኝ፣ ቊጣዬ በዚህ ስፍራ ይነድ ዳል፤ አይጠፋምም።’

26 እግዚአብሔርን ለመጠየቅ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ስለ ሰማኸው ቃል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

27 በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ስለአዋረድህ፣ እንዲሁም በእኔ ፊት ራስህን ዝቅ ስላደረግህ፣ ልብስህንም በመቅደድ በፊቴ ስለአለቀስህ፣ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር።