2 ዜና መዋዕል 34:27-33 NASV

27 በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ስለአዋረድህ፣ እንዲሁም በእኔ ፊት ራስህን ዝቅ ስላደረግህ፣ ልብስህንም በመቅደድ በፊቴ ስለአለቀስህ፣ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር።

28 እነሆ፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ በዓይንህ አታይም።’ ” መልሷንም ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።

29 ከዚያም ንጉሡ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሰበሰበ።

30 እርሱም ከትንሽ እስከ ትልቅ ካሉት ከይሁዳ ሰዎች፣ ከኢየሩሳሌም ሕዝብ፣ ከካህናትና ከሌዋውያን ጋር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ ለሕዝቡ አነበበላቸው

31 ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ ቆሞ፣ እግዚአብሔርን ይከተል ዘንድ በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ትእዛዛቱን፣ ሕግጋቱንና ሥርዐቱን ለመጠበቅ፣ በዚህ መጽሐፍ ለተጻፈውም የኪዳን ቃል ለመታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ።

32 ከዚህ በኋላ በኢየሩሳሌምና በብንያም የሚኖረው ሁሉ በዚህ ነገር ቃል እንዲገባ አደረገ፤ የኢየሩሳሌምም ሕዝብ የአባቶቹ አምላክ ባዘዘው የአምላክ ቃል ኪዳን መሠረት ፈጸሙ።

33 ኢዮስያስም አስጸያፊ ጣዖታትን ሁሉ ከመላው የእስራኤል ግዛት አስወገደ፤ በእስራኤል የነበሩትም ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ፤ እርሱ በሕይወት እያለም የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ አላሉም።