2 ዜና መዋዕል 35:13-19 NASV

13 እነርሱም የፋሲካውን መሥዋዕት በሥርዐቱ መሠረት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸት፣ በሰታቴና በድስት ቀቀሉ፤ ወዲያውኑም ለሕዝቡ አደሉ።

14 ከዚህ በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ ዝግጅት አደረጉ፤ ምክንያቱም ካህናቱ የአሮን ልጆች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን እስከ ሌሊት ድረስ ያቀርቡ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ዝግጅት አደረጉ።

15 መዘምራኑ የአሳፍ ዘሮች በዳዊት፣ በአሳፍ፣ በኤማንና በንጉሡ ባለ ራእይ በኤዶታም በተሰጠው መመሪያ መሠረት በቦታቸው ነበሩ። በእያንዳንዱ በር ላይ የነበሩት በር ጠባቂዎችም ሌዋውያን ወገኖቻቸው ስላዘጋጁላቸው፣ ከጥበቃ ቦታቸው መለየት አያስፈልጋቸውም ነበር።

16 በዚህ ዓይነት የፋሲካን በዓል በማክበርና የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ በማቅረብ የእግዚአብሔር አግልግሎት ሁሉ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በዚያኑ ቀን ተከናወነ።

17 በዚያን ጊዜ በስፍራው የተገኙ እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ የቂጣንም በዓል እንደዚሁ ሰባት ቀን አከበሩ።

18 ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ወዲህ እንዲህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመላው ይሁዳና ከእስራኤል፣ በዚያ ከነበሩትም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር እንዳከበረው አድርጎ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም።

19 ይህ ፋሲካ የተከበረው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንኛው ዓመት ነበር።