2 ዜና መዋዕል 36:10-16 NASV

10 በጸደይም ወራት ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ በእግዚአብሔ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ዕቃዎች ጋር ወደ ባቢሎን ወሰደው። የዮአኪንንም አጎት ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።

11 ሴዴቅያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ።

12 እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊትም ራሱን ዝቅ አላደረገም።

13 እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ እንጂ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም።

14 ከዚህም ላይ የካህናቱና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ፣ አስጸያፊ የሆኑትን የአሕዛብን ልማዶች በመከተልና በኢየሩሳሌም የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማርከስ፣ ባለ መታመናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ ሄዱ።

15 የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ፣ መልእክተኞቹን ይልክ ነበር፤

16 እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።