2 ዜና መዋዕል 4:4-10 NASV

4 በርሜሉ በዐሥራ ሁለት ኮርማዎች ላይ የቆመ ሲሆን፣ ኮርማዎቹም ሦስቱ ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። በርሜሉ በእነዚህ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ የሁሉም ጀርባ ወደ መካከል የዞረ ነበር።

5 የበርሜሉ ውፍረት አንድ ስንዝር፣ ከንፈሩ ደግሞ የጽዋ ከንፈር ወይም የሱፍ አበባ ይመስል ነበር፤ ይህም ሦስት ሺህ የባዶስ መስፈሪያ የሚይዝ ነበር።

6 እንዲሁም ዐሥር የመታጠቢያ ገንዳዎች አሠርቶ አምስቱን በደቡብ፣ አምስቱን ደግሞ በሰሜን በኩል አስቀመጠ፤ ገንዳዎች ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡት ነገሮች የሚታጠቡባቸው ሲሆኑ፣ በርሜሉ ግን ለካህናት መታጠቢያ የሚያገለግል ነበር።

7 በተሰጠው የአሠራር መመሪያ መሠረት፣ ዐሥር የወርቅ መቅረዞች ሠርቶ ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት፣ አምስቱን በስተ ደቡብ፣ አምስቱን በስተ ሰሜን አኖራቸው።

8 ዐሥር ጠረጴዛ ሠርቶም ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት አምስቱን በስተ ደቡብ፣ አምስቱን ደግሞ በስተ ሰሜን በኩል አኖራቸው፤ ደግሞም አንድ መቶ ጐድጓዳ የወርቅ ሳሕኖች ሠራ።

9 የካህናቱንም አደባባይ ሠራ፣ እንዲሁም ታላቁን አደባባይና በሮቹን ከሠራ በኋላ በናስ ለበጣቸው።

10 በርሜሉንም ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ ምሥራቅ ባለው ማዕዘን በቀኝ በኩል አኖረው።