2 ዜና መዋዕል 5:1-7 NASV

1 ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራው ሥራ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፣ ዕቃዎቹንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አኖራቸው።

2 ከዚያ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የየነገዱን መሪዎች ሁሉና የእስራኤላውያንን የቤተ ሰብ አለቆች በኢየሩሳሌም ሰበሰበ።

3 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ የሰባተኛው ወር በዓል በሚከበርበት ጊዜ፣ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ።

4 የእስራኤል ሽማግሌዎች በተሰበሰቡም ጊዜ ሌዋውያኑ ታቦቱን አነሡት፤

5 ታቦቱን፣ የመገናኛ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን የተቀደሱ ዕቃዎች ሁሉ ይዘው ወደ ላይ ወጡ፤ ሌዋውያን የሆኑ ካህናትም ተሸከሟቸው።

6 ንጉሥ ሰሎሞንና በአጠገቡ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ ስፍር ቊጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች በታቦቱ ፊት ሠዉ።

7 ካህናቱም የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ሆነው ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት።