2 ከዚያ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የየነገዱን መሪዎች ሁሉና የእስራኤላውያንን የቤተ ሰብ አለቆች በኢየሩሳሌም ሰበሰበ።
3 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ የሰባተኛው ወር በዓል በሚከበርበት ጊዜ፣ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ።
4 የእስራኤል ሽማግሌዎች በተሰበሰቡም ጊዜ ሌዋውያኑ ታቦቱን አነሡት፤
5 ታቦቱን፣ የመገናኛ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን የተቀደሱ ዕቃዎች ሁሉ ይዘው ወደ ላይ ወጡ፤ ሌዋውያን የሆኑ ካህናትም ተሸከሟቸው።
6 ንጉሥ ሰሎሞንና በአጠገቡ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ ስፍር ቊጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች በታቦቱ ፊት ሠዉ።
7 ካህናቱም የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ሆነው ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት።
8 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ከታቦቱ በላይ ባለው ስፍራ ላይ ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ሸፈኑ።