2 ዜና መዋዕል 6:34-40 NASV

34 “ሕዝብህ አንተ በምትልካቸው ቦታ ሁሉ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥኻት ወደዚህች ከተማ፣ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ወደዚህ ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩ፣

35 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ የጠየቁህንም አድርግላቸው።

36 “መቼም የማይበድል ሰው የለምና፣ አንተን በበደሉህ ጊዜ፣ ተቈጥተሃቸው ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር በምርኮ ለሚወስዳቸው ጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣

37 በተማረኩበት አገር ሆነው የልብ ጸጸት ተሰምቶአቸው ንስሐ ቢገቡና በምርኮ ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ቢሉ፣

38 ተማርከው በሚኖሩበትም ምድር ሆነው በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹምም ነፍሳቸው ቢመለሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ አንተም ወደ መረጥኻት ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣

39 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ በማደሪያህ ስማ፤ የጠየቊህንም አድርግላቸው። የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል።

40 አሁንም አምላኬ ሆይ፤ በዚህ ስፍራ ወደ ቀረበው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፣ ጆሮዎችህም የሚያደምጡ ይሁኑ።