2 ዜና መዋዕል 7:16-22 NASV

16 ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤተ መቅደስ መርጫለሁ፤ ቀድሸዋለሁም። ዓይኖቼም ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።

17 “አንተም ደግሞ አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ በፊቴ ብትሄድ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ ሥርዐቶቼንና ሕግጋቴን ብትጠብቅ፣

18 ለአባትህ ለዳዊት፣ ‘ከዘርህ እስራኤልን የሚገዛ አታጣም’ ብዬ በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት የመንግሥትህን ዙፋን አጸናለሁ።

19 “እናንተ ግን እኔን ከመከተል ተመልሳችሁ የሰጠኋችሁን ሥርዐቴንና ትእዛዜን ብትተው፣ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታገለግሉና ብታመልኩ፣

20 በዚያን ጊዜ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድሬ እነቅላቸዋለሁ፤ ለስሜ የቀደስሁትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ፤ በሕዝቦችም ሁሉ ዘንድ መተረቻና መዘባበቻ አደርገዋለሁ።

21 ይህ ቤተ መቅደስ አሁን እጅግ የሚያስደንቅ ቢሆንም በአጠገቡ የሚያልፉ ሁሉ በመገረም፤ ‘እግዚአብሔር በዚህች ምድርና በዚህ ቤተ መቅደስ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያመጣው ከቶ ለምን ይሆን?’ ይላሉ፤

22 ሕዝቡም፣ ‘ይህን ሁሉ ጥፋት ያመጣባቸው፣ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ሌሎችን አማልክት ስለ ተከተሉ፣ ስላመለኳቸውና ስላገለገሏቸው ነው’ ብለው ይመልሳሉ።”