2 ዜና መዋዕል 9:1-7 NASV

1 የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው ወደ ኢየሩሳሌም መጣች። ቅመማ ቅመም፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮችን በግመሎች አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ደረሰች፤ ወደ ሰሎሞንም ቀርባ በልቧ ያለውን ሁሉ አጫወተችው።

2 ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ሊመልስላት የተሳነው አንዳች ነገር አልነበረም።

3 የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብና የሠራውን ቤተ መንግሥት፣

4 በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አስተናባሪዎቹንና አለባበሳቸውን፣ ጠጅ አሳላፊዎቹንና አለባበሳቸውን እንዲሁም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ባየች ጊዜ እጅግ ተደነቀች።

5 ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስለ ሥራህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ሁሉ እውነት ነው።

6 ነገር ግን መጥቼ በዓይኔ እስካየሁ ጊዜ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ በርግጥም የጥበብህ እኩሌታ እንኳ አልተነገረኝም፤ እኔ ከሰማሁት ዝና እጅግ ትልቃለህ።

7 ሰዎችህ ምንኛ ታድለዋል! ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ ምንኛ ታድለዋል!