2 ዜና መዋዕል 9:11-17 NASV

11 ንጉሡም የሰንደሉን እንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ ደረጃ መሥሪያ እንደዚሁም ለመዘምራኑ የመሰንቆና የበገና መሥሪያ አደረገው፤ ይህን የመሰለ ነገር በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም።

12 ንጉሥ ሰሎሞን ለሳባ ንግሥት የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ስጦታውም እርስዋ ካመጣችለት በላይ ነበር። ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ አገሯ ተመለሰች።

13 ሰሎሞን በየዓመቱ የሚቀበለው ወርቅ ክብደቱ ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት ነበር።

14 ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር፤ እንዲሁም መላው የዐረብ ነገሥታትና የገዛ ምድሩ አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር።

15 ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ የተሠራ ታላላቅ ጋሻዎች አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበር።

16 እንዲሁም ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎች በጥፍጥፍ ወርቅ ሠራ፤ በእነዚህም በእያንዳንዳቸው የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖራቸው።

17 ከዚያም ንጉሡ በዝሆን ጥርስ ያጌጠና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ትልቅ ዙፋን ሠራ።