13 ሰሎሞን በየዓመቱ የሚቀበለው ወርቅ ክብደቱ ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት ነበር።
14 ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር፤ እንዲሁም መላው የዐረብ ነገሥታትና የገዛ ምድሩ አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር።
15 ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ የተሠራ ታላላቅ ጋሻዎች አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበር።
16 እንዲሁም ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎች በጥፍጥፍ ወርቅ ሠራ፤ በእነዚህም በእያንዳንዳቸው የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖራቸው።
17 ከዚያም ንጉሡ በዝሆን ጥርስ ያጌጠና በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ትልቅ ዙፋን ሠራ።
18 ዙፋኑ ስድስት መውጫ መውረጃ ደረጃዎች ሲኖሩት፣ ከዙፋኑ ጋር የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሆኖም ከመደገፊያዎቹም አጠገብ አንዳንድ አንበሳ ቆሞ ነበር።
19 እንዲሁም በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር ላይ አንዳንድ አንበሳ፣ ባጠቃላይ አሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር ተሠርቶ አያውቅም።