1 የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣“ደስ አያሰኙኝም”የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።
2 ፀሓይና ብርሃን፣ጨረቃና ከዋክብት ሳይጨልሙ፣ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፣
3 ቤት ጠባቂዎች ሲርዱ፣ብርቱዎች ሲጐብጡ፣ጥቂት በመሆናቸው ፈጪታዎች ሲያቆሙ፣በመስኮት የሚያዩትም ሲፈዙ፣
4 ወደ አደባባይ የሚያወጡ በሮች ሲዘጉ፣ወፍጮ ሟልጦ ድምፁ ሲላሽ፣ሰው በወፍ ድምፅ ሲነሣ፣ዝማሬው ሁሉ ሲዳከም፤
5 ዳገት መውጣት ሲያርድ፣መንገድም ሲያስፈራ፣የለውዝ ዛፍ ሲያብብ፣አንበጣም ራሱን ሲጐትት፣ፍላጎት ሲጠፋ፤በዚያም ጊዜ ሰው ወደ ዘላለማዊ ቤቱ ይሄዳል፤አልቃሾችም በአደባባዮች ይዞራሉ።