መክብብ 2:11-17 NASV

11 ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም።

12 ከዚያም ጥበብን፣እብደትንና ሞኝነትን ለመመርመር ሐሳቤን መለስሁ፤አስቀድሞ ከተደረገው በቀር፣ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል?

13 ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ ሁሉ፣ጥበብም ከሞኝነት እንደሚበልጥ ተመለከትሁ።

14 የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል፤ሆኖም የሁለቱም ዕድል ፈንታ፣አንድ መሆኑን ተገነዘብሁ።

15 ከዚያም በልቤ፣“የሞኙ ዕድል ፈንታ በእኔም ላይ ይደርሳል፤ታዲያ ጠቢብ በመሆኔ ትርፌ ምንድን ነው?” አልሁ።በልቤም፣“ይህም ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ።

16 ጠቢቡም ሰው እንደ ሞኙ ለዘላለም አይታወስምና፤በሚመጡት ዘመናት ሁለቱም ይረሳሉ።ለካ፣ ጠቢቡምእንደ ሞኙ መሞቱ አይቀርም!

17 ስለዚህ ከፀሓይ በታች የሚሠራው ሥራ አሳዛኝ ስለ ሆነብኝ ሕይወትን ጠላሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።