1 ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ። ለመስማት መቅረብ የሰነፎችን መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ እነርሱ ክፉ እንደሚሠሩ አያውቁምና።
2 በአፍህ አትፍጠን፤በእግዚአብሔርም ፊት ማንኛውንም ነገር ለመናገር፣በልብህ አትቸኵል፤እግዚአብሔር በሰማይ፣አንተ ደግሞ በምድር ነህ፤ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን።
3 በሥራ ብዛት ሕልም እንደሚታይ፣ብዙ ቃል ባለበትም የሞኝ ንግግር ይገለጣል።
4 ለእግዚአብሔር ስእለትን በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፤ በሰነፎች ደስ አይለውምና፤ ስእለትህን ፈጽም።
5 ስእለት ተስሎ ካለመፈጸም፣ አለመሳል ይሻላል።
6 አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። እግዚአብሔር በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ?
7 ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ፍራ።