ነህምያ 2:2-8 NASV

2 ስለዚህ ንጉሡ፣ “ሳትታመም ፊትህ ለምን እንዲህ ዐዘነ? መቼም ይህ የልብ ሐዘን እንጂ ሌላ አይደለም” አለኝ።እኔም በጣም ፈርቼ ነበር፤

3 ለንጉሡም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር፤ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ስትፈርስ፣ በሮቿም በእሳት ሲቃጠሉ ለምን ፊቴ አይዘን?” አልሁት።

4 ንጉሡም፣ “ታዲያ ምን ትፈልጋለህ?” አለኝ። ከዚያም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ፤

5 ለንጉሡም፣ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆንና ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፣ እንደ ገና እንድሠራት አባቶቼ ወደ ተቀበሩባት ወደ ይሁዳ ከተማ እንድሄድ ይፈቀድልኝ” አልሁት።

6 ከዚያም ንጉሡ አጠገቡ ከተቀመጠችው ንግሥት ጋር በመሆን፣ “ጒዞህ ምን ያህል ቀን ይፈጃል? መቼስ ትመለሳለህ?” ሲል ጠየቀኝ። ንጉሡም እኔን ለመስደድ ደስ አለው፤ እኔም ጊዜውን ወሰንሁ።

7 ደግሞም እንዲህ አልሁት፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ይሁዳ እስክደርስ ድረስ በደኅና እንዲያሳልፉኝ ከኤፍራጥስ ማዶ ላሉት አገረ ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤

8 እንዲሁም ለንጉሡ ደን ጠባቂ ለአሳፍ፣ በቤተ መቅደሱ አጠገብ ላለው ግምብ በሮች፣ ለከተማዪቱ ቅጥርና እኔም ለምገባበት ቤት ሠረገላ የሚሆን እንጨት እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይጻፍልኝ፤” መልካሚቱ የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ ነበረችና ንጉሡም ፈቀደልኝ።