አስቴር 3:1-7 NASV

1 ከዚህም ነገር በኋላ ንጉሥ ጠረክሲስ የአጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከሌሎቹም መኳንንት ሁሉ ከፍተኛውን ሥልጣን በመስጠት አከበረው።

2 ንጉሡ ስለ እርሱ ይህ እንዲደረግለት አዞ ስለ ነበር፣ በንጉሡ በር ያሉት የመንግሥቱ ሹማምት ሁሉ ለሐማ ተንበርክከው እጅ በመንሣት አክብሮታቸውን ይገልጡለት ነበር። መርዶክዮስ ግን ወድቆ አልሰገደለትም፤ አክብሮትም አላሳየውም።

3 ታዲያ በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን፣ “የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ?” ሲሉ ጠየቁት።

4 ይህንንም በየቀኑ ይነግሩት ነበር፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም። አይሁዳዊ መሆኑን ነግሮአቸው ስለ ነበር፣ የመርዶክዮስ ባሕርይ እስከ መቼ ሊቀጥል እንደሚችል ለማየት ሲሉ ይህንኑ ለሐማ ነገሩት።

5 ሐማም መርዶክዮስ ወድቆ እንዳልሰገደለትና እንዳላከበረው ሲያይ እጅግ ተቈጣ።

6 ይልቁንም መርዶክዮስ ከእነማን ወገን መሆኑን በተረዳ ጊዜ፣ መርዶክዮስን ብቻ መግደል እንደ ኢምንት ቈጠረው፤ ስለዚህ ሐማ በመላው የጠረክሲስ መንግሥት ውስጥ የሚገኙትንና የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድ ሁሉ ለማጥፋት ዘዴ ፈለገ።

7 ንጉሥ ጠረክሲስ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር፣ ቀኑንና ወሩን ለመለየት ፉር የተባለ ዕጣ ሐማ ባለበት ጣሉ፤ ዕጣውም አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ላይ ወደቀ።