1 ሰባተኛው ወር በደረሰ ጊዜ፣ እስራኤላውያን በየከተሞቻቸው ሳሉ፣ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆነው በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።
2 ከዚያም የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱና ካህናት ዘመዶቹ እንዲሁም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የሥራ ባልደረቦቹ፣ በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ፣ የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ መሥራት ጀመሩ።
3 በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ የተነሣ ፍርሀት ቢያድርባቸውም፣ መሠዊያውን በቀድሞው መሠረት ላይ ሠሩ፤ በመሠዊያውም ላይ ጠዋትና ማታ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ።
4 ከዚያም ለእያንዳንዱ ቀን እንደታዘዘው፣ በሚያስፈልገው ቊጥር ልክ የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ የዳስ በዓልን በተጻፈው መሠረት አከበሩ።