ዕዝራ 8:18-24 NASV

18 መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በእኛ ላይ ስለ ነበረች፣ ከሞሖሊ ዘሮች የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ የሆነውን ሰራብያ ተብሎ የሚጠራውን አስተዋይ ሰው፣ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንት የሚሆኑ ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን፤

19 እንዲሁም ሐሸብያንና ከሜራሪ ዘሮች የሻያን፣ ከወንድሞቹና ከአጎቶቹ ወንዶች ልጆች ጋር 20 ወንዶችን አመጡልን።

20 በተጨማሪም ዳዊትና ሹማምቱ ሌዋውያኑን እንዲረዳ ካቋቋሙት ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ቡድን 220 አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየስማቸው ተመዘገቡ።

21 ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጒዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ።

22 “መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቊጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር።

23 ስለዚህ ጾምን፤ ወደ አምላካችንም ስለዚህ ነገር ልመና አቀረብን፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ።

24 እኔም ከዋና ዋናዎቹ ካህናትም ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፣ ከእነርሱም ጋር ሰራብያን፣ ሐሸቢያንና ከወንድሞቻቸውም መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ፤