ዘካርያስ 11:2-8 NASV

2 የጥድ ዛፍ ሆይ፤ ዝግባ ወድቋልና አልቅስ፤የከበሩትም ዛፎች ጠፍተዋል!የባሳን ወርካዎች ሆይ፤ አልቅሱ፤ጥቅጥቅ ያለው ደን ተመንጥሮአል!

3 የእረኞችን ዋይታ ስሙ፤ክብራቸው ተገፎአልና፤የአንበሶችን ጩኸት ስሙ፤ጥቅጥቅ ያለው የዮርዳኖስ ደን ወድሟል!

4 እግዚአብሔር አምላኬ እንዲህ ይላል፤ “ለዕርድ የተለዩትን በጎች አሰማራ፤

5 የገዟቸው ያርዷቸዋል፤ ሳይቀጡም ይቀራሉ፤ የሸጧቸውም፣ ‘እግዚአብሔር ይመስገን፤ ባለጠጋ ሆኛለሁ’ ይላሉ፤ ጠባቂዎቻቸውም እንኳ አይራሩላቸውም።

6 ከእንግዲህ በምድሪቱ ለሚኖረው ሕዝብ አልራራምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ምድሪቱን ያስጨንቃሉ፤ እኔም ከእጃቸው አላድናቸውም።”

7 ስለዚህ ለዕርድ የተለዩትን በጎች፣ በተለይም የተጨቈኑትን አሰማራሁ። ሁለት በትሮች ወስጄም፣ አንዱን “ሞገስ” ሌላውንም “አንድነት” ብዬ ጠራኋቸው፤ መንጋውንም አሰማራሁ።

8 በአንድ ወር ውስጥ ሦስቱን እረኞች አስወገድሁ።በጎቹ ጠሉኝ፤ እኔም፣ ሰለቸኋቸው፤