6 ከእንግዲህ በምድሪቱ ለሚኖረው ሕዝብ አልራራምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ምድሪቱን ያስጨንቃሉ፤ እኔም ከእጃቸው አላድናቸውም።”
7 ስለዚህ ለዕርድ የተለዩትን በጎች፣ በተለይም የተጨቈኑትን አሰማራሁ። ሁለት በትሮች ወስጄም፣ አንዱን “ሞገስ” ሌላውንም “አንድነት” ብዬ ጠራኋቸው፤ መንጋውንም አሰማራሁ።
8 በአንድ ወር ውስጥ ሦስቱን እረኞች አስወገድሁ።በጎቹ ጠሉኝ፤ እኔም፣ ሰለቸኋቸው፤
9 “እረኛችሁ አልሆንም፤ የሚሞቱት ይሙቱ፤ የሚጠፉት ይጥፉ፤ የቀሩትም አንዱ የሌላውን ሥጋ ይብላ” አልኋቸው።
10 ከዚያም ከአሕዛብ ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን ለማፍረስ፣ “ሞገስ” ብዬ የጠራሁትን በትሬን ወስጄ ሰበርሁት።
11 በዚያም ቀን ኪዳኑ ፈረሰ፤ ሲመለከቱኝ የነበሩትና የተጨነቁት በጎችም የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ዐወቁ።
12 እኔም፣ “የሚበጅ መስሎ ከታያችሁ ዋጋ ዬን ክፈሉኝ፤ አይሆንም ካላችሁም ተውት” አልኋቸው፤ ስለዚህ ሠላሳ ብር ከፈሉኝ።