ዘካርያስ 12:1-7 NASV

1 ስለ እስራኤል የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ ሰማያትን የዘረጋ፣ ምድርን የመሠረተ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

2 “ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሚያንገደግድ ጽዋ አደርጋታለሁ፤ ይሁዳም እንደ ኢየሩሳሌም ሁሉ ትከበባለች።

3 የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርሷ ላይ በሚሰበሰቡበት በዚያ ቀን፣ ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ የማይነቃነቅ ዐለት አደርጋታለሁ፤ ለማነቃነቅ የሚሞክሩ ሁሉ ራሳቸውን ይጐዳሉ።

4 በዚያን ቀን እያንዳንዱን ፈረስ በድንጋጤ፣ የተቀመጡባቸውንም ሰዎች እብደት እመታለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “የይሁዳን ቤት በዐይኔ እጠብቃለሁ፤ ነገር ግን የአሕዛብን ፈረሶች ሁሉ አሳውራለሁ።

5 የይሁዳ መሪዎች በልባቸው፣ ‘የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ብርቱ ናቸው፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ጸባኦት ነውና’ ይላሉ።

6 “በዚያ ቀን የይሁዳን መሪዎች በዕንጨት ክምር ውስጥ እንዳለ የእሳት ምድጃ፣ በነዶም መካከል እንዳለ የፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፤ በግራና በቀኝ ዙሪያውን ያሉትን ሕዝቦች ይበላሉ፤ ኢየሩሳሌም ግን ከስፍራዋ ንቅንቅ አትልም።

7 “የዳዊት ቤትና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ክብር ከይሁዳ ክብር እንዳይበልጥ እግዚአብሔር በመጀመሪያ የይሁዳን መኖሪያዎች ያድናል።