ዘካርያስ 14:10-16 NASV

10 ምድር ሁሉ ከጌባ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሬሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች።

11 የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች።

12 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጒድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ።

13 በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል።

14 ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል።

15 ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችን፣ በቅሎዎችን ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሶች ሁሉ ይመታል።

16 ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ።