ዘካርያስ 14:12-18 NASV

12 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጒድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ።

13 በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል።

14 ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል።

15 ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችን፣ በቅሎዎችን ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሶች ሁሉ ይመታል።

16 ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ።

17 የምድር ሕዝብ ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ከሆነ ዝናብ አያገኙም።

18 የግብፅም ሰዎች ወደዚያ ሳይወጡ ቢቀሩ፣ ዝናብ አያገኙም፤ እግዚአብሔር ወጥተው የዳስ በዓልን በማያከብሩ አሕዛብ ላይ የሚያደርሰውን መቅሠፍት በእነርሱም ላይ ያመጣል።