ዘዳግም 1:17-23 NASV

17 በፍርድ አድልዎ አታድርጉ፤ ትልቁንም ትንሹንም እኩል እዩ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ማንኛውንም ሰው አትፍሩ። ከዐቅማችሁ በላይ የሆነውን ሁሉ ወደ እኔ አምጡት፤ እኔ አየዋለሁ።”

18 በዚያን ጊዜ ማድረግ የነበረባችሁን ሁሉ ነገርኋችሁ።

19 ከዚያም አምላካችን እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘን መሠረት ከኮሬብ ተነሥተን እንዳያችሁት በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ ዐልፈን፣ በኰረብታማው በአሞራውያን አገር በኩል ወደ ቃዴስ በርኔ መጣን።

20 እኔም፣ እንዲህ አልኋችሁ፤ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ወደ ኰረብታማው የአሞራውያን አገር ደርሳችኋል፤

21 እነሆ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ምድሪቱን ሰጥቶአችኋል፤ አሁንም የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በነገራችሁ መሠረት ውጡ፤ ውረሷትም፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም።”

22 ከዚያም ሁላችሁ ወደ እኔ መጥታችሁ፣ “ምድሪቱን እንዲሰልሉልን ሰዎች አስቀድመን እንላክ፤ እነርሱም ወደዚያ የሚያደርሰንን መንገድና የምንሄድባቸውን ከተሞች በማጥናት ተመልሰው ይነግሩናል” አላችሁ።

23 ይህም ሐሳብ መልካም መስሎ ታየኝ፤ እኔም ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በማድረግ ከእናንተ ዐሥራ ሁለት ሰዎች መረጥሁ።