ዘዳግም 12:3-9 NASV

3 መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።

4 በእነርሱ መንገድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አታምልኩ።

5 ዳሩ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ።

6 ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ።

7 በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።

8 ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤

9 ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም።