ዘዳግም 15:1-7 NASV

1 በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት አድርግ።

2 አፈጻጸሙም እንደሚከተለው ነው፤ እያንዳንዱ አበዳሪ ለእስራኤላዊ ባልንጀራው ያበደረውን ይተውለት፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የዕዳ ምሕረት አውጆአልና፣ አበዳሪው፣ እስራኤላዊ ባልንጀራውን ወይም ወንድሙን ዕዳውን እንዲከፍለው አይጠይቀው።

3 ለባዕድ ያበደርኸውን መጠየቅ ትችላለህ፤ ወንድምህ ከአንተ የተበደረውን ማናቸውንም ዕዳ ግን ተወው።

4 ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፣ በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤

5 ይህ የሚሆነውም ለአምላክህለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፈጽመህ ስትታዘዝና ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ስትከተል ብቻ ነው።

6 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ስለሚባርክህ፣ አንተ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ እንጂ ማንም አንተን አይገዛህም።

7 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ላይ ካሉት ከተሞች ባንዲቱ ውስጥ ድኻ ቢኖር፣ በድኻ ወንድምህ ላይ ልብህን አታጨክንበት፤ ወይም እጅህን ወደ ኋላ አትሰብስብበት።