ዘዳግም 16:11-17 NASV

11 አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ በመካከልህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበላችሁ።

12 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህንንም በጥንቃቄ ጠብቅ።

13 የእህልህን ምርት ከዐውድማህ፣ ወይንህንም ከመጭመቂያህ ከሰበሰብህ በኋላ፣ የዳስን በዓል ሰባት ቀን አክብር።

14 በበዓልህ አንተ፣ ወንድና ሴት ልጅህ፣ ወንድና ሴት አገልጋይህ፣ በከተማው ያለ ሌዋዊ፣ መጻተኛ፣ አባት አልባውና መበለቲቱ ደስ ይበላችሁ።

15 እግዚአብሔር (ያህዌ) በመረጠው ስፍራ ለአምላክህለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በዓሉን ሰባት ቀን አክብር፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእህል ምርትህና በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክሃል፤ ደስታህም ፍጹም ይሆናል።

16 ወንዶችህ ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ፣ በቂጣ በዓል፣ በመከር በዓልና በዳስ በዓል ላይ፣ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ይቅረቡ፤ ማንም ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ባዶ እጁን አይቅረብ።

17 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን እያንዳንዱ እንደ ችሎታው ይስጥ።