ዘዳግም 16:4-10 NASV

4 በምድርህ ሁሉ ላይ በአንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዋውም ላይ ማናቸውንም ሥጋ ጧት ድረስ እንዲቈይ አታድርግ።

5 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ በማናቸውም ከተማ ፋሲካን መሠዋት አይገባህም፤

6 ነገር ግን ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ፣ ፀሓይ ስትጠልቅ ምሽቱ ላይ ከግብፅ በወጣህበት ሰዓት ዓመታዊ መታሰቢያ በዚያ ፋሲካን ሠዋ።

7 ሥጋውንም ጠብሰህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብላ፤ ሲነጋም ወደ ድንኳንህ ተመልሰህ ሂድ።

8 ስድስት ቀን ያልቦካ ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የተቀደሰ ጉባኤ አድርግ፤ ሥራም አትሥራበት።

9 እህልህን ማጨድ ከምትጀምርበት ዕለት አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቊጠር፤

10 ከዚያም በኋላ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን፣ በፈቃድህ የምታመጣውን ስጦታ በማቅረብ በመከሩ በዓል አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አክብር።