ዘዳግም 16:7-13 NASV

7 ሥጋውንም ጠብሰህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብላ፤ ሲነጋም ወደ ድንኳንህ ተመልሰህ ሂድ።

8 ስድስት ቀን ያልቦካ ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የተቀደሰ ጉባኤ አድርግ፤ ሥራም አትሥራበት።

9 እህልህን ማጨድ ከምትጀምርበት ዕለት አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቊጠር፤

10 ከዚያም በኋላ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን፣ በፈቃድህ የምታመጣውን ስጦታ በማቅረብ በመከሩ በዓል አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አክብር።

11 አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ በመካከልህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበላችሁ።

12 አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህንንም በጥንቃቄ ጠብቅ።

13 የእህልህን ምርት ከዐውድማህ፣ ወይንህንም ከመጭመቂያህ ከሰበሰብህ በኋላ፣ የዳስን በዓል ሰባት ቀን አክብር።