8 በአንድ የነፍስ ግድያ ዐይነትና በሌላ፣ በአንድ ዐይነት ሕጋዊ ክርክርና በሌላ፣ ወይም በአንድ የክስ ዐይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጒዳይ ቢነሣ፣ ከዐቅምህ በላይ የሆነ ጒዳይ በከተሞችህ ውስጥ ቢያጋጥምህ፣ ተነሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ፤
9 ካህናት ወደሆኑት ሌዋውያንና በዚያን ጊዜ ዳኛ ወደ ሆነው ሰው ሄደህ፣ ስለ ጒዳዩ ጠይቃቸው፤ እነርሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል።
10 አንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡህ ውሳኔ መሠረት ፈጽም፤ እንድ ትፈጽም የሚሰጡህን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርግ።
11 በሚያስተምሩህ ሕግና በሚሰጡህ መመሪያዎች መሠረት ፈጽም። እነርሱ ከሚነግሩህ ቀኝም ግራም አትበል።
12 አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ለማገልገል በዚያ የሚቆመውን ካህን ወይም ዳኛ የሚንቅ ይገደል፤ ከእስራኤልም መካከል ክፉውን አስወግድ።
13 ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲሰማ ይፈራል፤ ከዚያ ወዲያም እንዲህ ያለውን የንቀት ድርጊት አይደግመውም።
14 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፣ በምትወርሳትና በምትቀመጥባት ምድር፣ “በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ፣ እኔም በላዬ ንጉሥ ላንግሥ” ብትል፣