1 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ምድራቸውን ለአንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ በሚደመስሳቸው ጊዜና አንተም እነርሱን አስለቅቀህ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጥበት ጊዜ፣
2 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር አማካይ ስፍራ፣ ሦስት ከተሞችን ለራስህ ለይ።
3 ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር መንገዶችን ሠርተህ፣ በሦስት ክፈላቸው።
4 በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው።
5 እነሆ፤ አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንጨት ለመቊረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፣ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፣ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል።
6 አለበለዚያ በተንኰል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፣ መንገዱ ረጅም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና፣ መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል።