ዘዳግም 22:16-22 NASV

16 የልጂቱም አባት ለአለቆቹ እንዲህ ይበል፤ “ልጄን ለዚህ ሰው ዳርሁለት፤ እርሱ ግን ጠላት፤

17 ስሟንም በማጥፋት፣ ‘ልጅህን ከነድንግልናዋ አላገኘኋትም’ ብሎኛል፤ ነገር ግን የልጄ ድንግልና ማረጋገጫ ይኸውላችሁ፤” ከዚያም ወላጆቿ የደሙን ሸማ በከተማዪቱ አለቆች ፊት ይዘርጉት።

18 ከዚያም በኋላ አለቆቹ ሰውየውን ይዘው ይቅጡት፤

19 ይህ ሰው የአንዲት እስራኤላዊት ድንግል ስም አጥፍቶአልና አንድ መቶ ሰቅል ብር ያስከፍሉት፤ ገንዘቡንም ለልጂቱ አባት ይስጡት፤ ሴቲቱም ሚስቱ ሆና ትኖራለች፤ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊፈታት አይችልም።

20 ሆኖም ክሱ እውነት ሆኖ ሴቲቱ ድንግል ለመሆኗ ምንም ማረጋገጫ ማቅረብ ካልተቻለ፣

21 ገና በአባቷ ቤት ሳለች በማመንዘር በእስራኤል ውስጥ ወራዳ ተግባር ፈጽማለችና ወደ አባቷ ቤት ደጃፍ ያምጧት፤ እዚያም የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሯት። ክፉውን ከመካከልህ ማስወገድ አለብህ።

22 አንድ ሰው፣ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፣ አብሮአት የተኛው ሰውና ሴቲቱ ሁለቱም ይገደሉ፤ ክፉውን ከእስራኤል ማስወገድ አለብህ።