ዘዳግም 24:1-7 NASV

1 አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት።

2 ከቤቱ ከወጣች በኋላ ሌላ ባል ብታገባ፣

3 ሁለተኛ ባሏም እንደዚሁ ጠልቷት የፍቺ ወረቀት በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ቢሰዳት ወይም ቢሞት፣

4 ከዚያ በኋላ የፈታት የመጀመሪያ ባሏ፣ የረከሰች በመሆኗ እንደ ገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አስጸያፊ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኀጢአት አታምጣ።

5 አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፣ ለጦርነት አይሂድ፤ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሠራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ እቤቱ ይቈይ፤ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት።

6 ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፣ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና።

7 አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።